top of page

            የደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አመሰራረት እና የጉዞ ሂደት (ታሪክ)

 

             ስለ ኦክላንድ ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አመሰራረትና የጉዞ ሂደት ታሪክ ስናነሳ ለቤተ ክርስቲያኒቷ መመስረት እግዚአብሔር ምክንያት ያደረጋቸውን ሃይማኖታዊ ፍቅርና መልካም ራዕይ የነበራቸውን ካህናትና ምዕመናን ማስታወስ ተገቢ ነው ። እግዚአብሔር ሥራውን በሰዎች ላይ አድሮ ይሰራልና በነዚህ ቅን ወገኖች የተመሰረተችው ቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ ወቅቶች የተነሱ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፋ በእግዚአብሔር ፈቃድ እዚህ ደረጃ ደርሳ ማየታችን ለእኛ በውስጡ ላለፍን ሁሉ እጅግ አስደሳች በመሆኑ ለዚህ ክብር እንድንበቃ ላደረገን ቸሩ አምላካችን ምስጋና እናቀርባለን።

             

              የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን መቋቋም መነሻ ምክንያት በወቅቱ በአካባቢው በነበሩት አባት መልአከ ምህረት አባ ተክለ ሃይማኖት ተገኝ እና (በወቅቱ ዲያቆን) ቀሲስ ሞላ ታደሰ የቅዱስ ሚካኤል ጽዋ ማህበር ተመስርቶ ሲካሄድ በሁዋላ ወደ ቤተ ክርስቲያንነት እንዲያድግ በማኅበርተኞቹ ስለተወሰነ በወቅቱ የሰሜን አሜሪካ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት (ያሁኑ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያትክ) አቡነ ማትያስ ተጠይቀው አባታዊ ቡራኬያቸውን በመስጠት የኦካላንድ ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካአል ቤተ ክርስቲያ ተብሎ እንዲሰየም በደብዳቤ ፈቅደው በእለተ ሆሳዕና በሚያዚያ 6 1997 ዓም ወይንም Aril 14, 2005 እኤአ ተከፈተ ። በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ሆነው ስለተመደቡ ኅዳር 03 1998 ወይንም November 12 ቀን በ2005 እኤአ በአካል ቡራኬያቸውን ከመስጣቸውም በተጨማሪ መንበረ ጵጵስናቸውን በዚሁ ቤተ ክርስቲያን አድርገው ለተወሰነ ጊዜ ቆይተዋል: ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለሀገረ ስብከታችን የተመደቡ በፁዓን አባቶች በቦታዉ በመገኘት ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል።

             

               ይሁን እንጅ: ቤተ ክርስቲያናችን: በአካባቢው የኑሮ ውድነትና የቤተ ክርስቲያኑ የገንዘብ አቅም አለመኖር ምክንያት የራሱ የሆነ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን (ቋሚ አገልግሎት መስጫ ቦታ) በቀላሉ ማግኘት ባለመቻሉ የመጀመሪያዉን አገልግሎት የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያኝ ተከራይቶ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ጀመረ።

             

               ቤተ ክርስቲያናችን ለረጅም ዘመናት ህንጻ ቤተ ክርስቲያን በመከራየት ህዝበ ክርስቲያኑን ስታገለግል ቆይታለች። ሆኖም ከአራት አመታት በላይ ስንገለገልበት የነበረው ህንጻ ባለቤቶች ለሃይማኖታችን በማይመች መልኩ ሁኔታዎችን በመቀየራቸው ቦታውን መልቀቃችን ግዴታ ሆነ። ይህንን ተከትሎ በተደረገው አጠቃላይ ማኅበረ ምእመናን ስብሰባ ፤ ሌላ ቦታ እንከራይ ወይስ የራሳችን ህንጻ ቤተ ክርስቲያን እንግዛ ፧ በሚለው ሃሳብ ላይ በሰፊው ከተወያየ በሁዋላ ፤ የራሳችን ህንጻ ቤተ ክርስቲያን መግዛት ይሻለናል በሚለው ሃሳብ ጠቅላላ ጉዔው በሙሉ ድምጽ ወሰነ ። ሰበካ ጉባዔውም ይህን ጉዳይ ተከታተሎ የሚያስፈጽም ከሰበካ ጉባዔ ፣ ከህንጻ ኮሚቴ ፣ ከልማት ክፍልና ከሰንበት ትምህርት ቤት የተውጣጣ ልዩ ኮሚቴ አቋቋመ ። ኮሚቴዉም ፤ የህንጻ ቤተ ክርስቲያን ከማፈላለጉ ጎን ለጎን የገንዘብን አቅምን 6 Page 6 ለማጠናከር የሚረዳ ልዩ የምሳ መርሃ ግብር አዘጋጅቶ ከ140 ሺህ በላይ ዶላር ከማስገግኘቱም በተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ ያላቸው ምእመናን አንዲያበድሩ በማስተባበር ከ መቶ ሺህ ዶላር እንዲገኝ አስችሉዋል።

             

               ለረጅም ጊዜ የሚሸጥ ህንጻ ሲያፈላልግ ከቆየ በሁዋላ ፤ በመጨረሻም ይህን የምታዩትን ህንጻ አንዳገኘ ፤ የህግ ፣ የሪል እስቴትና የሂሳብ ሙያ ያላቸውን ምእመናን በማስተባበር ካስጠና በሁዋላ በ 1.65 ሚሊዮን ዶላር አንዲገዛ አድርጓል ። ህንጻው እንደተገዛም ፤ የሰበካ ጉባዔው አስተዳደር ከምህንድስና ጋር የተያያዘ ሙያውና ልምዱ ያላቸውን አባላት ያከተተ የቴክኒክ ኮሚቴ አደረጀ ። ኮሚቴዉም አጠቃላይ ህንጻውን ለእኛ አገልግሎት በሚመች መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፤ አስተካክሎ አሳምሮ በማዘጋጀት ለዚህ ክብር እንድንበቃ አድርጎናል ። ቤተ ክርስቲያናችንንም ከ50,000 ዶላር በላይ ወጪ ማዳን ችሉዋል ። ሁሉን በጊዜው ለሚሰራው አምላክ ክብር ምስጋና ይሁን።

ሳምንታዊ አገልግሎቶች

ሥርዓተ ቅዳሴ

ከ7 AM - 9:30 AM

ትምህርተ ወንጌል

ከ 9:30 AM - 10:30 AM

ያግኙን

አድራሻ

678 26th st.

Oakland, CA 

94612 USA

ኢሜል

dmkm510@gmail.com

መልዕክቶችን ለማግኘት ይመዝገቡ
  • Grey YouTube Icon
  • Grey Facebook Icon
bottom of page