ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን
ሥርዓተ ጥምቀት

ጥምቀት የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲተረጉሙ “ጥምቀት” በቁሙ፡- “ማጥመቅ፣ መጠመቅ፣ አጠማመቅ፣ ጠመቃ፣ የማጥመቅና የመጠመቅ ሥራ፣ ኅፅበት፣ በጥሩ ውኃ የሚፈጸም” በማለት ተርጉመውታል። ጥምቀት አንድ ምዕመን እንደገና ከመንፈስ ቅዱስ ልደት የሚያገኝበትና የቤተ ክርስቲያን አባል የሚሆንበት የመጀመሪያው መግቢያ በር ነው። ምሥጢረ ጥምቀትን የመሠረተው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በዮሐንስ ወንጌል ፫፣ ፭ ላይ “እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፣ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አትደነቅ” በማለት የአይሁድ አለቃ ለነበረው ለኒቆዲሞስ ጌታችን ያስተማረውን ትምህርት ልብ ላለው ጥምቀት በጌታችን ትምህርት መመሥረቷን ይስረዳል።
በሰው ልጅ ዘላለማዊ ድኅነት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ሥርዓተ ጥምቀት ከሌሎቹ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በቀዳሚነት የሚፈጸምና የማይደገም ሥርዓት ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “አንዲት ጥምቀት” በማለት የሥርዓተ ጥምቀትን አለመደገም ገልጦ ተናግሯል (ኤፌ.፬፣ ፭)። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቦ እንደሚገኘው፥ በቁስጥንጥንያ በ ፫፻፹፩ ዓ.ም. የተሰበሰቡ ፩፻፶ የሃይማኖት አባቶቻችን “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት፣ ኃጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” በማለት የጥምቀትን አንድ መሆንና ኃጢአትን በደልን የምታርቅ ስለመሆኗ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናግረዋል፤ ሃይማኖታቸውንም ገልጠዋል።

