ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት ከዘመነ ሐዋርያት ጊዜ ጀምሮ እስከ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ዜና ወንጌል ተሰበከ እንጂ የተደራጀ ክህነታዊ አገልግሎት አልነበረም። ሆኖም በዚሁ ወቅት በቅዱሳን ሐዋርያት እንደተመሠረቱት ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ኢየሩሳሌም በተሰበሰበው የመጀመሪያው የሐዋርያት ሲኖዶስ በተላለፈው ቀኖና እና ሲያያዝ በመጣው የሐዲስ ኪዳን የሥርዓት መጻሕፍት ትተዳደር ነበር።
በቆስጠንጢኖስ ዘመነ መንግሥት በኒቅያ ጉባኤ (፫፻፳፭ ዓ.ም.) የተሰበሰቡ ሃይማኖታቸው የቀና ፫፻፲፰ ሊቃውንት (ሠለስቱ ምዕት) ከሐዋርያት ሲኖዶስ ሲያያዝ የመጣውን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት አድርገው ለቤተክርስቲያንና ለሀገር አስተዳደር እንዲጠቅም ብለው ፍትሐ ነገሥት የተሰኘውን የሕግ መጽሐፍ አዘጋጅተው ለንጉሡ ለቆስጠንጢኖስ ሰጡት። ፍትሐ ነገሥት ሥርወ ቃሉ ግዕዝ ሲሆን ቃል በቃል ሲፈታ የነገሥታት ፍርድ ማለት ነው። ይኸውም ክርስቲያን ነገሥታት ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ሀገርን የሚያስተዳድሩበት ወይም ፍርድ/ፍትሕ የሚሰጡበት የሕግ መጽሐፍ ነው። ከታላቁ ቆስጠንጢኖስ ጀምሮ ክርስቲያን ነገሥታት ፍትሐ ነገሥትን ለቤተክርስቲያንና ለሀገር ማስተዳደሪያ ሕግ አድርገው መጠቀም ጀምረዋል። በሀገራችን በኢትዮጵያም የመጀመሪያው ጳጳስ አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን የኒቅያ ጉባኤ (፫፻፳፭) አፈ ጉባኤ በነበረው በቅዱስ አትናቴዎስ ተሹሞ ወደ አክሱም ሲመጣ ፍትሐ ነገሥትን ጨምሮ ብዙ የሥርዓት መጻሕፍትን ይዞ ስለመጣ አብርሃ ወአጽብሃ (ነገሥታተ ኢትዮጵያ) ሀገሪቷንም ቤተ ክርስቲያኒቷንም በፍትሐ ነገሥት ያስተዳድሩ ነበር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአብርሃ ወአጽባሃ ዘመነ መንግሥት ከአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን (፫፻፴ ዓ.ም.) ጀምሮ በቅርብ ጊዜ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት (፲፱፻፵፱ ዓ.ም.) የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ በሥራ ላይ እስከዋለበት ጊዜ ድረስ ወደ ፩ሺ፮፻ ዓመታት ያህል ሀገሪቱም ሆነች ቤተ ክርስቲያኒቱ የሚመሩበት ሕግ ፍትሐ ነገሥት (ፍትሕ መንፈሳዊና ፍትሕ ሥጋዊ) ነበር።
ቃለ ዓዋዲ የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ በ፲፱፻፵፱ ዓ.ም. ለቤተ መንግሥት ከተዘጋጀ ከ16 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ኅብረት በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንድትደራጅ ታስቦ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ፕትርክና በትእዛዝ አዋጅ ቁጥር 85/65 ተፈቅዶ ጥቅምት 15 ቀን 1965 ዓ.ም. በሥራ ላይ ዋለ።ቃለ ዓዋዲ የሚለው ሐረግ መሠረተ ቃሉ የግዕዝ ሲሆን ቃል በቃል ሲፈታ የአዋጅ ነጋሪ ቃል ማለት ነው። ይኸውም በነቢያት ትንቢት የተነገረውን (ኢሳ፤40፡3) ኋላም የጌታን የመምጣቱን አዋጅ እየተናገረ በመጣው በመጥምቁ ዮሐንስ የተፈጸመውን (ማቴ፤3፡1-17) የንስሐ ጥሪ፣ የመንግሥተ ሰማያት አዋጅ መሠረት አድርጐ የተሰየመ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አዋጅ ነው። አንድ መንግሥት ሕዝቡን የሚያስተዳድርበት በግልጽ በአዋጅ የሚነገር ሕግ አለው። እንደዚሁ ሁሉ ቃለ ዓዋዲም በምድር የእግዚአብሔር ቤተ መንግሥት የሆነች፣ የመንግሥተ ሰማያት በር፣ የሰማይ ደጅ የምትባል፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጥምቀት ከእግዚአብሔር ተወልደው ዜጐቿ የሆኑ ክርስቲያኖች የሚተዳደሩበት የቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ሕግ ነው። ይህም ዋናውን የእግዚአብሔር ሕግ (ወንጌለ መንግሥትን) መሠረት በማድረግ ለዘመኑ በሚበጅ መልኩ የተዘጋጀ የቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ሕግ ነው። ስለዚህ ቃለ ዓዋዲ በኋላ ዘመን የተፈጠረ ሳይሆን የቤተክርስቲያን አመራርና አስተዳደር በኢየሩሳሌም በተደረገው የሐዋርያት ጉባኤ (ሐዋ፤15፡32) ተመክሮና ተወስኖ በተላለፈው ሕግና ሥርዓት በማኅበረ ካህናቱና ምእመናኑ ጠቅላላ ጉባኤ በተመረጡ ቅዱስ መንፈስ ባደረባቸው ኃላፊዎች (ሐዋ፤6፡1-7) ሥራ አስፈጻሚነት ይካሄድ የነበረውን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ ነው (ቃለ ዓዋዲ ገጽ 1)። ይህ ቃለ ዓዋዲ (የቤተክርስቲያን አስተዳደር አዋጅ) ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅምት 15 ቀን 1965 ዓ.ም. በሥራ ላይ ከዋለ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን ሳይለቅ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ እንደጊዜው ሁኔታ ሚያዚያ 19/1970፣ ታህሣሥ 10/1974፣ ግንቦት 9/1977፣ ግንቦት 10/1991 ተሻሻሏል።

